የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤንች ሸኮ ህዝቦች የባህል ማእከል ግንባታ የሚሆን ቦታ አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤንች ሸኮ ህዝቦች የባህል ማእከል ግንባታ የሚሆን ቦታ አበረከተ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የባህል ማዕከል መገንቢያ የሚሆን ቦታ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በዛሬውም እለት የከተማ አስተዳደሩ ለቤንች ሸኮ ህዝቦች የባህል ማዕከል ግንባታ የሚሆን የቦታ ርክክብ አድርጓል።
በዚሁ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ “አዲስ አበባ የሁላችንም ቤት የሁላችንም ከተማ ናት፤ መዲናችሁ እንዲህ ደምቃችሁ ስታደምቋት ከፍተኛ ደስታ ይሰማታል” ብለዋል።
“እንዲህ ሰብሰብ ስንል እናምራለን” ያሉት ከንቲባ አዳነች፥ በማማር ከመድመቅም አልፎ እናስፈራለንም ብለዋል፡፡
የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በመዲናቸው ላይ የባህል መገንቢያ ቦታዎች እየተዘጋጁ ሲሰጥ መቆየቱን ከንቲባ አዳነች አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃነት መገለጫ፣ እጅግ ደማቅና እርስ በእርስ የተሳሰሩ ማንነቶችና ባህሎች ያሏት ሃገር መሆኗን ገልፀው፥ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሞከሩ የተለያዩ ሙከራዎችን ማሸነፍ የቻለች አገር ናት ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው፥ “የአዲስ አበባ ከተማ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች መሰብሰቢያ፣ የሁላችንም ቤት የሁላችንም ጓዳ የሆነች ከተማ ነች” ማለታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዞኑ ልማት ማህበር የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ አስመልክቶ ያቀረበውን ጥያቄ የከተማው አስተዳደር በፍነጥት አይቶ ምላሽ መስጠት በመቻሉ አመስግነዋል።