አቶ ፍቃዱ ተሰማ በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ በአርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ፡፡
ኃላፊው በመልዕክታቸው ፥ በኪነ-ጥበቡ ዓለም ለትውልድ ደማቅ አሻራን ያሳረፈው ታለቁን የሀገር ባለውለታ አርቲስት ዓሊ ቢራን በማጣታችን የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል።
አርቲስት ዓሊ ቢራ ፥ ከዘመን ዘመን የማይደበዝዝ የገሀዱን ዓለም እውነታ በኪነ-ጥበብ አዋዝቶ ትውልድ የሚማርበትን አሻራ አኑሮ ማለፍ ከመቃብር በላይ መኖር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አርቲስቱ ፥ የእድሜ ዘመን የፍቅር አምባሳደር፣ የሚሊዮኖች ተምሳሌት፣ በሚስረቀረቀው መረዋ ድምፁ በብዙዎች ህሊና ውስጥ በዕንቁ ቀለም የተፃፈ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ ህያው ሆነው በክብር የሚወረሱ፣ የክፍለ ዘመናችን የኦሮምኛ ሙዚቃ ክስተት፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ማማ፣ ከጫፍ ጫፍ የተወደደና የተከበረ የኢትዮጵያዊነት ምልክ፣ ስለአንድነት ስለ ፍቅር ስለ እውነት የኖረ ትንታግ እንደነበረም ነው ያነሱት፡፡
“ሀቲ ቴኛ ተካ ማልቱ አዳን ኑ ባሴ?” (የአንድ እናት ልጆች ነን ምንድነው የለያየን?!) በማለት አበክሮ የጠየቀ ታላቅ ውርስና ቅርስ የነበረ አርቲስት ነውም ብለዋል ኃላፊው።
ታላቁ የኪነ-ጥበብ ሰው አርቲስት ዓሊ ቢራ በተስረቅራቂው ድምፁ የተጠበባቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ቋንቋን ማወቅና አለማወቅ፣ ባህል፣ የአኗኗር ሁኔታና የህዝቦች ስነ-ልቦና ሳይገድባቸው በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ በፍቅር የሚደመጡና ‘’ሙዚቃ ቋንቋ ነው’’ የተሰኘውን አባባል በተጨባጭ ያረጋገጡ ናቸውም ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ፥ ስለሆነም አርቲስት ዓሊ ቢራ አይቀሬዉ የተፈጥሮ ክስተት ሆኖ በሞት ብናጣውም በድንቅ የኪነ-ጥበብ ስራዎቹ በትውልድ ቅብብሎሽ ዘላለም እየተዘከረ የሚኖር ታላቅ የሀገር ባለውለታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አርቲስት ዓሊ ቢራ ዘመን በማይሽረው የሙዚቃ ስራዎቹ ሁለገብ የሆነ አስተምህርሆችን ጥሎልን አልፏልም ነው ያሉት።
ተደምጦ በማይጠገብ አንደበቱ ስለፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነት በማቀንቀን አዎንታዊ የሆነ ማህበራዊ መስተጋብር የሚሳለጥበትን እውነታ አሳይቷል ፤ ጥላቻና “ዘረኝነት በልብህ ካለ ገና መኖር አልጀመርክም” በማለት ጥላቻን የኮነነ ድነቅ የኪነጥብ ሰዉ እንደሆነም አንስተዋል።
በህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ዙርያ ያቀነቀናቸው ሙዚቃዎቹ በተለይም በኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ትግል ታሪክ በደማቅ ቀለም የሚፃፉ፣ የእኩልነት ትግል ማንቂያ ሆነው ያታገሉ በትውልዱ ቅብብሎሽ የሚዘከሩ ደማቅ አሻራ ናቸውም ብለዋል።
በመሆኑም ታላቁ የኪነጥበብ አባት አርቲስት ዓሊ ቢራ በኪነ-ጥበብ ብቻ ሳይሆን በነፃነት ትግሉም በቀደምትነት እንደሚጠቀስ ነው ያወሱት፡፡
ሁለገብ የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ ሥራዎቹ ተዘርዝረው የማያልቁ፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም የሚያስተምሩ ቋሚ ሀውልት ናቸው ያሉት ኃላፊው ፥ ትውልድ በቅብብሎሽ እየተማረበት ዓሊን ይዘክርበታል ብለዋል።
አሊ ቢራን ማጣት ከባድ ሀዘን ቢሆንም ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ስራዎቹ ትውልድ ይገነባልና ዘላለም እየዘከርነዉ እንፅናናለን ብለዋል።
አቶ ፈቃዱ ለአርቲስት ዓሊ ቢራ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለጥበብ አድናቂዎቹ መጽናናትን ተመኝተዋል፡