ዳሽን ባንክ ባለፈው በጀት አመት 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሽን ባንክ በ2014 ዓ.ም የባንክ ኢንዱስትሪውን የሚፈትኑ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በበጀት አመቱ መጨረሻ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል።
ባንኩ 29ኛ መደበኛ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት÷ ትርፉ ባለፈው በጀት አመት ከተገኘው የ57 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የገለጸው።
በበጀት አመቱ 16 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን የጠቀሰው ባንኩ፥ የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 91 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ከፍ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል።
ከዚህ ውስጥም በሸሪክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ነው ተብሏል።
ዳሽን ባንክ በበጀት አመቱ ጠቅላላ የሃብት ክምችቱን 117 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ማድረስ መቻሉ ተነግሯል።
ይህም ካለፈው በጀት አመት ሲነጻጸር የ24 በመቶ ብልጫ እንዳለው እና የባንኩን የተከፈለ ካፒታል 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማድረስ እንደቻለም ነው የተገለጸው፡፡
ባንኩ የብድር ክምችቱን ወደ 79 ቢሊየን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፥ማህበራዊ ሃላፊትን ከመወጣት አንጻር ትምህርት ቤቶችን፣ የውሃ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መገንባቱ ተጠቅሷል።
የዲጂታል ባንኩን ከማስፋት አንጻርም የአሞሌ ባንኪንግን በማሳደግ የተጠቃሚውን መጠን 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ማድረስ ችሏል።
በሃይማኖት ኢያሱ