የኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ በፍጥነት እየተዛመተ ነው – ዶክተር ቴድሮስ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው ከታወቀበት እለት ጀምሮ የመጀመሪያዎቹ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ለመያዝ 67 ቀናት መውሰዱን ገልጸዋል።
ቀጣዮቹ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ለመያዝ 11 ቀናትን ወስዷል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ሶስተኛ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ በአራት ቀናት ውስጥ ብቻ መያዛቸውን በመጥቀስ የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት አሳሳቢነት አመላክተዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በመግለጫቸው ቫይረሱን ለመከላከል የቡድን 20 አባል ሃገራት መሪዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቀርባለሁም ብለዋል።
በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ 350 ሺህ ሰዎች ዓለም ላይ ሲያዙ፥ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉት ለህልፈት ተዳርገዋል።
100 ሺህ አካባቢ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸው ተገልጿል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision