የ12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ ሂደት ስኬታማ እንደነበር ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የፈተና አስተዳደርና አሰጣጥ ችግርን ለመፍታት በመንግስት በተሰጠው አመራር ፈተናው በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ዙር ለ937 ሺህ ተማሪዎች የሰጠውን የ12 ክፍል ብሄራዊ ፈተና መጠናቀቅና የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህም ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት ውስጥ 98 ነጥብ 9 በመቶዎቹ በዩኒቨርሲቲዎች ቀርበው ፈተናቸውን እንዲወስዱ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን፥ ፈተናውም በጥራትና በጥንቃቄ መሰጠቱ ተመላክቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ በአራት ዩኒቨርሲቲዎች ከ12 ሺህ በላይ ተፈታኞች “ፈተናውን አንፈተንም” ያሉ ተማሪዎች በመደበኛው የፈተና አሰጣጥ በሚቀጥለው ዓመት ፈተና መውስድ አይችሉም ብለዋል፡፡
ሌላው በተለያዩ የጤና ችግሮች የ3 ተማሪዎች ህይወት ማለፍ ፣በመንገድ ላይ ባጋጠመው የመኪና አደጋ የአንድ ተማሪ ህይወት መጥፋትም በፈተናው ወቅት ያጋጠመ ክስተት እንደነበር ተነስቷል።
ፈተና ለመኮራረጅ የሞከሩ፣ የተከለከሉ ቁሶችን ይዘው የገቡና የፀጥታ ችግር ለመፍጠረ የሞከሩም እንደነበሩ የተገለፀ ሲሆን፥ የፈተና ደንብ ተላልፈው ለተገኙ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው መደረጉም ተገልጿል።
ሌላው በመግለጫው በአደጋና በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ፈተናውን መውሰድ ያልቻሉ ተፈታኞች ከ1 ወር በኋላ ፈተናውን እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተመላክቶ ፈተናቸውን ከወሰዱ በኃላ አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።
በትዕግስት ብርሃኔ