ኩረጃን ለማስቀረት “የፀረ- ኩረጃ ኮፍያዎች” የተጠቀመው የፊሊፒንሱ ኮሌጅ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፊሊፒንስ የሚገኝ አንድ ኮሌጅ ተማሪዎቹ በፈተና ወቅት እንዳይኮራረጁ ለተማሪዎች የሰጠው መመሪያ መነጋጋሪያ ሆኗል።
ሌጋዝፒ በተሰኘችው ከተማ የሚገኘው ይህ ኮሌጅ ኩረጃን ለማስቀረት ለተማሪዎች ያልተለመደ መመሪያ አውጥቷል።
ኮሌጁ ተማሪዎችን ከካርቶን፣ ጥቅም ላይ ከዋሉ የእንቁላል ሳጥኖች እና ከሌሎች ቁሶች ኮፍያዎች እንዲሰሩ ነበር የጠየቀው።
ተማሪዎቹም ለጥያቄው ምላሽ መሥጠታቸው የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾችን ትኩረት እንዲስብ አድርጓል፡፡
ተማሪዎቻቸውን “ፀረ-ኩረጃ ኮፍያዎች” እንዲያዘጋጁ የጠየቁት ፕሮፌሰር ማንዳኔ የተባሉት መምህር ላልተለመደ ጥያቄያቸው ምክንያታቸውን ሲናገሩ “አዝናኝ በሆነ መልኩ” ሐቀኝነትን እና ታማኝነትን ለተማሪዎቼ የማሳይበትን መንገድ ስፈልግ ነበር ብለዋል፡፡
በቢኮል የምኅንድስና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ የሜካኒካል ምኅንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ሜሪ ጆይ ማንዳኔ-ኦርቲዝ በበኩላቸው ነገሩ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮሌጁ ተማሪዎችም የተለያዩ እና አዝናኝ ፀረ-ኩረጃ ኮፍያዎችን ተጠቅመው ጥቅምት ወር ላይ የሚወሰደውን የኮሌጁን የአጋማሽ ትምህርት ዘመን ፈተና መውሰዳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሮፌሰር ማንዳኔ ከዓመታት በፊት በታይላንድ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዶ መመልከታቸውን እና እርሳቸውም ለጠየቁት የፀረ-ኩረጃ ኮፍያ መነሻ ሃሳብ እንደሆናቸው ተናግረዋል።
የፊሊፒንሷ ፕሮፌሰር ማንዳኔ ይህንን ሃሳብ ለምህኅድስና ተማሪዎቻቸው ካቀረቡ በኋላ ተማሪዎቹ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በአቅራቢያቸው ከሚያገኟቸው ቁሳቁስ ሠርተው መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።