አሸባሪው ህወሓት ሶስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል – አምባሳደር አደም መሀመድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ሶስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብ እንደሚገባ በቱርክ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አደም መሀመድ ገለጹ።
አምባሳደር አደም መሀመድ በኢትዮጵያ ወቅታዊና ሀገራዊ ሁኔታ ላይ “አፍሪካ ኮርድናሲዮን ቪ-ኢጂቴም መርከዚ አከም” ከተሰኘ የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ በፊትና ከለውጥ በኋላ ያሳለፈቻቸውን ስኬትና ፈተናዎች አብራርተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ግጭት አሸባሪው ህወሓት ከ20 ዓመታት በላይ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ በነበረው የሀገር መካለከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸሙ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ጦርነቱን ባጠረ ጊዜ ለመቋጨት ካለው ጽኑ ፍላጎት ባሻገር በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ዜጎቹ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስታውሰዋል።
በጊዜ ሂደትም የትግራይ ክልል ህዝብ መደበኛ የእርሻና ተያያዥ ተግባራቱን ማከናወን እንዲችል የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ የሀገር መካለከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱን አውስተዋል።
ለትግራይ ህዝብ የተሰጠውን የሰላም እድል እንደመልካም አጋጣሚ የተጠቀመው አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች በከፈተው ሁለተኛ ዙር ጦርነት ከፍተኛ ወረራ በመፈጸም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መሞከሩን ጠቁመዋል።
የሽብር ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ የተላከ ሰብዓዊ ድጋፍ በመዝረፍ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አመላላሽ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት በመጠቀም በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት በመፍጠር ፣ በህዝቡ ላይ ግፍ መፈጸሙንም ማስታወሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
መንግስት ግጭቱን በሰላም ለመቋጨት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የሚመሩት የሰላም አማራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።
አሸባሪው ህወሐት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ሶስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን ጠቅሰው መንግስትም የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ጉዳዩ የሚያሳስባቸው አካላትም አሸባሪው ህወሓት ሀገርን ለማተራመስ ካለው ዓላማ አንጻር ጦርነቱን መክፈቱን በአግባቡ በመገንዘብ እንዲያወግዙት ጠይቀዋል።