በመጀመሪያው ሩብ አመት ከ93 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት ከ93 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የእቅድ፣ ክትትልና ግምገማ የስራ ሂደት ኃላፊ ተመስገን ተሰማ÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሀገር ውስጥና ከወጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ ከ93 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።
ሚኒስቴሩ በዘረጋቸው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አሰራሮች ግብር ከፋዮች በቀላሉ ግብር መክፈል መቻላቸው ገቢው እንዲጨምር አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሐሰተኛ ግብይቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር መጠናከር ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።