አቶ ደመቀ መኮንን እና የሶማሊያውን ጠ/ሚ ሃምዛ አብዲን ጨምሮ የጣና ፎረም ተሳታፊዎች ባህር ዳር ገቡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የጣና ፎረም ተሳታፊዎች ባህር ዳር ከተማ ገብተዋል፡፡
10ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ በአፍሪካ የሰላም፣ ጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር ሲሆን ÷ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡
በትናንትናው ዕለት የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፑን እና በርካታ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ተጋባዥ እንግዶች በፎረሙ ለመሳተፍ ባህርዳር መግባታቸው ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኤልሳዲግ አሊ እና ብሄራዊ ደህንነት ሀላፊ ሌተናል ጀኔራል አህመድ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎችም ተሳታፊ እንግዶች ባህር ዳር ገብተዋል።
መሪዎቹ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የአማራ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ እንዲሁም የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሃመድና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።