በምዕራብ አርማጭሆ 134 ኩንታል አደገኛ ዕፅ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ 134 ኩንታል አደገኛ ዕፅ መያዙን ፖሊስ ገለጸ፡፡
የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ፖሊስ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር እንዳልካቸው ተሰማ እንደገለፁት፥ ዕፁ የተያዘው በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች በመነሳት በአርማጭሆ ወረዳ በኩል ወደ ሱዳን ሊገባ ሲል በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል ነው፡፡
አደገኛ ዕፁ የሚዘዋወረው በሞተር ሳይክል እና በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ መሆኑን የተናገሩት ረዳት ኢንስፔክተር እንዳልካቸው ከተያዙ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት የተቀጣ ሲሆን የቀሪዎቹ የምርመራ መዝገብ ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ለፖሊስ የሚያደርገውን ድጋፍ እና መረጃ የመስጠት ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መገለፁን ከአማራ ፖሊስ ኮሚሽንያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡