Fana: At a Speed of Life!

ኅብረተሰቡ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ላበረከተው አስተዋጽዖ የጋራ ግብረ ኃይሉ አመሰገነ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የተከበሩ በዓላት ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቁ ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽዖ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ምስጋና አቅርቧል፡፡
 
የጋራ ግብረ ሃይሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷መላው ኅብረተሰብ ከጸጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት ጸጥታ እንዲጠበቅ ያደረገው ተሳትፎ በየአካባቢው የተከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት፣ የመስቀል ደመራ ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ ጉልህ አስተዋጽዖ በማበርከቱ የጋራ ግብረ ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል።
 
በመስቀል ደመራ በዓልና በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ወደ ሀገራዊ ቀውስ ኢንዲሸጋገር በአሸባሪዎች ሤራዎች ሲጠነሰሱ ነበር ብሏል።
 
ሆኖም ግን ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የሚያስተውላቸውን አጠራጣሪ ነገሮች በተመለከተ ለጸጥታና ለደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠቱ እንዲሁም በአደባባይ በዓላቱም ላይ የተመደቡ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እገዛ በማድረጋቸው በመላ ሀገሪቱ የተከበሩት የአደባባይ በዓላት ፍጹም ሰላማዊ ድባብ የሰፈነባቸው ሆነው ተጠናቅቀዋል።
ለዚህ ስኬትም መላው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ነው ያለው የጋራ ግበረ ሃይሉ።
 
በተለያዩ ግንባሮች ሽንፈት የተከናነቡ አሸባሪዎችና ተባባሪዎቻቸው በአደባባይ በዓላቱ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እንዳላቸው በጸጥታና ደኅንነት አካላት በመታወቁ ክትትል ሲደረግ ነበርም ብሏል።
 
በቂ መረጃና ማስረጃዎችም ከተሰበሰቡ በኋላ የሕወሓት፣ የሸኔና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት ጥቃት ለመፈጸም ካዘጋጇቸው የጦር መሣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
 
በዚህ ረገድ ኅብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉና የአደባባይ በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ያደረገው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድናቆት የሚገባው መሆኑን አንስቷል፡፡
 
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ሰላምን ለማረጋገጥና ጸጥታን ለማስፈን ብቁና ዝግጁ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው÷ ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ደኅንነቷን ለመጠበቅ በቂ ዝግጅት እንዳለው አረጋግጧል።
 
ኅብረተሰቡም ሰላምና ጸጥታ እንዲጠበቅ እያሳየ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.