ቴስላ ኩባንያ በርካታ ድርጊቶችን መከወን የሚችል ሮቦት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ቴስላ ኩባንያ በአንድ ጊዜ በርካታ ድርጊቶችን መከወን የሚችል ሮቦት ይፋ አድርጓል።
ሮቦቱ መራመድ፣ እጆቹን ማወዛወዝ እና በጣቶቹ ዕቃ መያዝ የሚችል መሆኑ ነው የተነገረው።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሎን መስክ÷ “ኦፕቲመስ” የሚል ስሜ የተሰጠው ሮቦቱ ከኩባንያው በተጨማሪ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊረዳ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ዓላማችን ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ ሮቦቶችን በየጊዜው ማስተዋወቅ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ሮቦቱ በፈረጆቹ 2027 ለገበያ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የመሸጫ ዋጋውም 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የተቆረጠለትመሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ሮቦቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከ 8 ወራት ያነሰ ጊዜ የፈጀ ሲሆን÷ ሮቦቱ ከተነገረለት በላይ በርካታ ሰራዎችን ማከናወን እንደሚችል መስክ አስረድተዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎች ስራዎችን ቀላል በማድረግ ይታወቃሉ ፤ነገር ግን የቴስላ ኩባንያ ሮቦቶች ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ማንኛውንም ስራ መስራት እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በቴስላ ኩባንያ ውስጥ የሚደረጉ የውስጥ የስራ ሂደቶች በአዲሱ ሮቦት የሚታገዙ መሆኑን እና ሮቦቱ ጥቅም ላይ የሚውልባቸው የስራ ዘርፎች ለወደፊት እየሰፉ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው ለወደፊትም ከሮቦት በተጨማሪ ለመኪና መገጣጠሚያ ከተሰሩ የሀርድዌር እና የሶፍትዌር ምርቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ጀልባዎችን ለመስራት ማቀዱን ሲኤንኢቲ ዘግቧል፡፡