Fana: At a Speed of Life!

ኢሬቻ እርስ በእርስ ስህተት ከመፈለግ ይልቅ መደማመጥን ያበረታታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢሬቻ እርስ በእርስ ስህተት ከመፈለግ ይልቅ መደማመጥን እንደሚያበረታታ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ኢሬቻ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን መሳብ የቻለ በዓል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ÷ ኢሬቻ በዘር፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሃይማኖትና በሌሎች መስፈርቶች አድልኦ ሳይደረግ ሁሉም ሰው ፈጣሪውን ለማመስገን የሚወጣበት በዓል መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ዛሬ ኢሬቻ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚያከብሩት ሥርዓት ሆኗልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር በወግ ባሕል እና እሴት የበለጸግን ሕዝቦች ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መቻቻልና አብሮ መኖርን የሚያበረታቱ ብዙ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አሉንም ብለዋል።

ኢሬቻ እርስ በእርስ ስህተት ከመፈለግ ይልቅ እርስ በርስ መደማመጥን እንደሚያበረታታም ነው ያነሱት።

ከሀዘን እና ጥላቻ ይልቅ ሰላም እና ፍቅርን እንደሚያጎላም አውስተዋል።

ኢሬቻ የሰላም መድረክ በመሆኑ በዓሉን የሚያከብሩ እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው ሥርዓቱን ከመፈጸማቸው በፊት እርስ በእርስ ሰላም ስለመሆናቸው እንዲሁም ፈጣሪያቸውን እና ተፈጥሮን ስላለመበደላቸው ማሰብ እንደሚኖርባቸውም አንስተዋል፡፡

ከዛም ወደ መልካ የሄደው የበዓሉ አክባሪ መልካውን በእርጥብ ሳር ከመንካቱ በፊት “ሰላም ነው” ብሎ ይመልሳል፤ በእርጥብ ሳሩ መልካውን ነክቶ መሬሆ መሬሆ በማለት ፈጣሪውን ያመሰግናልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

ኢሬቻን የሚያውቅ ሰው ቂምን ትቶ ሰላምን ይሰብካል፤ አንድነት እና ሰላምን ትብብር እና ወንድማማችነትንም ያጠናክራል ነው ያሉት።

ኢሬቻን የሚያውቅ ሰው ከፈጣሪ ላገኘው የከበረ ስጦታ እውቅና ይሰጣል፤ በተፈጥሮ ያለውን አንድነት እና አብሮ መኖር እያደነቀም ፈጣሪውን ያመሰግናል ብለዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.