ነፍሰ ጡሯ ውሻ አሳዳጊ ያጣችውን ጦጣ እያሳደገች ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህንድ አንድ ውሻ ወላጅ አልባ የሆነች ጦጣን ማሳደግ መጀመሯ ብዙዎቹን አስገርሟል።
የትንሿ ጦጣ እናት የአካባቢው ነዋሪዎች ሰብሎቻቸውን ከጦጣና ዝንጀሮ ለመከላከል በወሰዱት እርምጃ ተገድላለች።
ነፍሰ ጡር የሆነችው ውሻም ከአካባቢው ነዋሪዎች እርምጃ የተረፈችውንና አሳዳጊ አልባዋን ጦጣ መንከባከብ ጀምራለች።
ትንሿ ጦጣ እናቷ በአካባቢው ነዋሪዎች ስትገደል የአስር ቀን እድሜ ነበራት፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህም ባልተለመደ ወዳጅነት ውሻዋ እንደ ልጇ እየተንከባከበቻት ትገኛለች።
ጦጣ እና ውሻ በተፈጥሮ የማይስማሙ ቢሆንም የሁለቱ ግንኙነት ግን የአካባቢው ነዋሪዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
የሁለቱን ግንኙነት በፎቶግራፍ ያስቀረው የ48 ዓመቱ ፎቶግራፍ አንሺ ፕራክ ባድል የጦጣዋና የውሻዋ ፍቅር እንዳስገረመው ገልጿል።
ሁለቱ የተለያዩና የማይስማሙ ቢሆኑም ውሻዋ እናቷን ተክታ እያሳደገቻት መሆኑን ሳውቅ አስገርሞኛልም ብሏል።
ይህ ዓይነቱ ግንኙነት ከሌላ ወገን ወይም ሀይማኖት ስለሆነ ብቻ እርስ በርስ ለሚጣሉና ለሚገዳደሉ የሰው ልጆች ትልቅ ትምህርት ነውም ይላል ፕራንክ ባድል።
ምንጭ፡-ደይሊ ሜይል