Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ልዑካን ቡድን ጋር በክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥና ማስፋፊያ ዙሪያ  ተወያይተዋል፡፡

ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት÷  የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተለይም ባለፉት አመታት የክልሉን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፉ የክልሉን የከተማና የገጠር ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ከተያዙት 34 ፕሮጀክቶች ውስጥ 26 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት አመት በክልሉ ወጪ በ17 ሚሊየን ብር የፕሮጀክት ማስፋፊያ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

የክልሉን ኢኮኖሚ ከማሳደግና ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት አንጻር ፣ በገጠር ወረዳዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው÷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ፍላጎት ለሟሟላት የተለያዩ የማስፋፋፊያ ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ የክልሉን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በውይይቱ የክልሉ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.