Fana: At a Speed of Life!

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት የምዕራባውያን የማስገደድ እርምጃ አካል ነው – በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች በቅርቡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት ሪፖርት የምዕራባውያን የማስገደድ እርምጃ አካል መሆኑን በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ጆርጌ ለፈብሬ ኒኮላስ ተናገሩ።

አምባሳደሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ምዕራባውን ኢትዮጵያውያንን በማንበርከክ የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች መጣላቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ የሚደርስባትን ጫና ተቋቁማ የልማት ጥረቷን የምታጠናክርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት አምባሳደሩ።

የተመድን የነሐሴ 22 ሪፖርት የጠቀሱት አምባሳደሩ “ሪፖርቱ ሰነድ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር ያለመ ፖለቲካዊ መሳሪያ ነው” ብለዋል።

አያይዘውም በተመድ ውስጥ የሚገኙ ምዕራባውያን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየሰሩ እና የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ብቻ መሰል ሰነዶችን እያዘጋጁ መሆኑንም አመላክተዋል።

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የሚያሳድሩት ቀጣይነት ያለው ጫና ከስነ ምግባር ያፈነገጠ እና በኢትዮጵያ ላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችልም አብራርተዋል።

የኩባን ሁኔታ በማሳያነት የጠቀሱት አምባሳደሩ ማዕቀቡ የታዳጊ ሀገራት ህዝቦችን ህይወት አስከፊ ሁኔታ ላይ የሚጥል መሆኑንም አውስተዋል።

አያይዘውም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለቻቸው ማዕቀቦች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት የሚጎዳ መሆኑን አስረድተዋል።

ሀገራቸው በኢትዮጵያ ላይ በምዕራቡ ዓለም የሚጣሉ ማዕቀቦችን እንደምትቃወም በመጥቀስም፥ ኩባ የተመድን መድረክ ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በቆይታቸው ኢትዮጵያውያን ከዚያድባሬ ወራሪ ሰራዊት ጋር ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ ኩባ 15 ሺህ ወታደር መላኳን አስታውሰው፥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር በተካሄደው ጦርነት የኩባ ወታደሮች የህይወት መስዋዕልትነት መክፈላቸውንም ነው የጠቀሱት።

ከዚህ ባለፈም በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሀገራቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማገዝ ያላትን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

ኩባ ከኢትዮጵያ የቡና ልማት ዘርፍ ልምድ መውሰድ ትፈልጋለችም ነው ያሉት አምባሳደሩ።

ኢትዮጵያ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በርካታ ስኬቶች ማስመዝገቧን በማንሳትም፥ በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጠን በሚደረገው ሂደት ኩባ የድርሻዋን እንደምትወጣም ነው ያረጋገጡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.