ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል፡፡
በቅርቡ የአልጀዚራ ኔትወርክን የጎበኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ልኡካን ቡድን በዶሃ ከኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አብዱል ባሲጥ ጀማል ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ርዕሰ መምህሩ የኳታር መንግስት ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት መሬት በመስጠት እና ሙሉ በሙሉ በመገንባት እንዲሁም መኪናን ጨምሮ አጠቃላይ ወጪዎችን በመሸፈን ለማህበረሰቡ እንዲያገለግል ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
በኳታር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ ሀገር ልጆቻቸውን በመላክ እንዲያስተምሩ ይገደዱ እንደነበርም አስታውሰው፥ አሁን ወላጆች ልጆቻቸውን በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ካሪኩለም መሰረት ልጆቻቸውን በዶሃ በራሳቸው ትምህርት ቤት ማስተማር መቻላቸውን አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተጨማሪም በትምህርት ቤቱ 14 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እንደሚማሩ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ድጋፍ የተደረገው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዶሃን ከጎበኙ በኋላ ለኳታሩ ልዑል ሼክ ተሚም ቢን ሃማድ አል ሳኒ ያለውን ችግር ካስረዱ በኋላ ባቀረቡት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም ባለፉት ዓመታት በተደረገው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥረት መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት ቀጣይ እና መጠናከር ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሚር በድሩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!