የካፊቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የካፊቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር በተመድ የትምህርት የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የካፊቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በቦንጋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በበዓሉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ÷ ሥራን መሠረት አድርጎ የሚከበረው የካፊቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ የህዝቡን ታላቅነት እና ሥልጣኔ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የካፊቾ ብሔረሰብን ባሕል፣ ታሪክ እና ትውፊት ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ጥረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ÷ በዓሉን ስናከብር ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነው ጀግንነት እና የአካባቢያችንን ሠላም የማስጠቅ እና የተፈጥሮ ሐብት የማልማት ልምድ በማጠናከር ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የብሔረሰቡን የበዓል አከባበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
በተስፋዬ ሚሬሳ