የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ተመድ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ አደጋዎች በዓለም ላይ ዘርፈ ብዙ ቀውስ እያስከተሉ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ፡፡
ዓለም አቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት÷ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ዓለም ላይ በቀን 200 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ጉዳት እንደሚደርስ ጠቁሟል፡፡
ሪፖርቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎች ባለፉት 50 ዓመታት በአምስት እጥፍ እንደጨመሩም አመላክቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ችግር በአማካይ በቀን 115 ሰዎች ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑንም ነው የገለጸው።
አሁን ባለው ሂደትም ምድራችን እጅግ ከፍተኛውን የዓለም ሙቀት መጠን በቀጣዮቹ አምስት አመታት ውስጥ የማስተናገድ እድሏ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስጠንቅቋል።
የሰው ልጅ በፈጠረው የአየር ብክለት ምክንያት፥ ምድራችን ከፍተኛ ሙቀት፣ ሰደድ እሳት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅና ከባድ አውሎ ነፋስ፣ የእርሻ መሬት ለምነት ማጣት፣ በአፈር ውስጥ ያለው የአሲድ መጠን መብዛትና የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት መድረቅና የብዝሃ ህይወት መዛባት፣ ድርቅ እና በተዛባ የአየር ንብረት ምክንያት ስነ ምህዳራዊ ቀውስ እያተናገደች ትገኛለች ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም በመርዛማ አየር ምክንያት በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ የጤና ቀውስ እየተከሰተ መሆኑንም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ÷ በፓኪስታን የተከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሮፓውን የሙቀት ማዕበል፣ በቻይና፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በአሜሪካ የሚስተዋለውን ድርቅ አንስተዋል።
ለዚህም የድንጋይ ከሰልን ምርትንና የትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን “በካይነት” በዋና መንስኤነት ጠቅሰዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው ከቀን ቀን እየተባባሰ ለመጣው የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ምንም አይነት የተፈጥሮ ምክንያት እንደሌለ ማስገንዘባቸውንም ያሆ ኒውስ አስነብቧል፡፡