አዲሱ ዓመት ህወሓት የከፈተብንን ጦርነት ቀልብሰን ትላልቅ ድሎችን የምናስመዘግብበት ሊሆን ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 ህወሓት ለሦስተኛ ጊዜ የከፈተብንን ጦርነት ቀልብሰን ትላልቅ ድሎችን ለማስመዝገብ የምንሠራበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠላም፣ የብልጽግና፣ የዕድገት፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት አብሮነትንና ወንድማማችነትን በጽኑ መሠረት ላይ ገንብተን የኢትዮጵያን አንድነት እና ብልጽግና የምናረጋግጥበት ይሆናልም ብለዋል።
መንግስት ያቀረበውን የሠላም ጥሪ የገፋው አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት አንድነትታችንን በማጠናከር እንቀለብሰዋለን ያሉት አቶ አሻድሊ፥ ጦርነቱን በጋራ በመቀልበስ ትላልቅ ድሎችን ለማስመዝገብ የሚሠራበት አመት እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሉትን መልካም እሴቶች በመጠቀም ዘላቂ ሠላም ለመገንባትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሠራም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በመልዕክታቸው በመጠናቀቅ ላይ ባለው 2014 ዓ.ም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡