Fana: At a Speed of Life!

ምዕራባውያን በሩሲያ-ዩክሬን ጉዳይ ግጭት ቀስቃሽ ፖሊሲ እያራመዱ ነው – ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይ ላይ የሚከተሉት ፖሊስ የሁለቱን ሀገራት ግጭት ይበልጥ የሚያባብስ ነው ሲሉ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን ገለጹ፡፡
 
ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን ከሰርቢያ አቻቸው አሌክሳንደር ቩሲክ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
 
ፕሬዚዳንቱ ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ ምዕራባውያን በሩሲያ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት የተዛባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
 
ቱርክ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት በሞስኮ ላይ የሚያራምዱት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ትክክል አለመሆኑን በውል እንደምትገነዘብም አንስተዋል፡፡
 
ሀገራቱ በሩሲያ ላይ ግጭት ማባባስን መሰረት ያደረገ ፖሊስ ይከተላሉ ያሉት ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን÷ በዚህ የተዛባ ፖሊሲም ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
ለአብነትም ምዕራባውያን በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተጀመረውን ጦርነት ለማባበስ የተትረፈረፈ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እየለገሱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
በአንጻሩ አንካራ በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ እንደምትከተል ነው የገለጹት፡፡
 
ለዚህም ዩክሬን የስንዴ ምርቷን በጥቁር ባህር በኩል ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ ከሩሲያ ጋር በቱርክ አማካኝነት ስምምነት መፈረሙን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.