ያስመዘገብነውን የስንዴ ምርታማነት እያጠናከርን ከሄድን፥ በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለቀጣናችን የዳቦ ቅርጫት መሆን እንችላለን – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “እስካሁን ያስመዘገብነውን የስንዴ ምርታማነት እያጠናከርን እና እያስፋፋን ከሄድን፥ በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለቀጣናችን የዳቦ ቅርጫት መሆን እንችላለን” አሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ እየተከበረ ያለውን የአምራችነት ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው ይህን ያሉት።
በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ከመኸር እርሻ ምርት ስንዴን ጨምሮ ከሁሉም የሰብል ምርቶች፥ በአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደርና አርብቶ አደር 400 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል፡፡
በበልግ ወቅት እርሻ ምርት ደግሞ 2 ሚሊየን ሔክታር በማልማት 63 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም በበጋ መስኖ ምርት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተያዘው ሀገራዊ ዕቅድ ለመተግበር በበጋ መስኖ 36 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ዕቅድ ተይዟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕመድ ከዚህ በፊት እንደገለጹትም፥ የማይታረሱ መሬቶችን በማረስ በኩታ ገጠም እርሻ በስንዴ ምርት እራሳችንን ለመቻል ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
የግብርና ልማት የዕድገት መሠረት በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን እና በግብዓትና በገበያ ትስስር ውጤታማ እንዲሆን ይደረጋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡