የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ በመሆናቸው ተቋማቱን ዘግቶ ተማሪዎቹን ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ እየተወሰዱ ካሉ ጥንቃቄዎች አኳያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መታመኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህም ወደየመጡበት አካባቢ በሚሄዱበት ጊዜ በጉዟቸው ለቫይረሱ የመጋለጣቸው እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለሚታመን ነውም ብሏል።
ስለሆነም ባሉበት ሆነው ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰጡ መመሪያዎችን ተከትለው ጥንቃቄ በማድረግ በመምህራኖቻቸው የሚሰጡ ንባቦችን እያካሄዱ ለ2 ሳምንታት እንዲቆዩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም
1. ለተማሪዎች አስፈላጊው ክትትል ይደረግ
2. ፊት ለፊትና በክፍል የሚሰጡ ትምህርቶችን በማስቀረት ለተማሪዎች የተዘጋጁ መማሪያ ጽሁፎች፣ ማጣቀሻ መፅሐፍት፣ የመፅሐፍት ቅጂዎች እና በኢንተርኔት የሚቀርቡ ፅሁፎችን በበቂ ደረጃ በማቅረብ እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በግላቸው/ በመኝታ ክፍላቸው ሆነው እንዲያነቡ፣ መምህራን በኢሜይልና በተለያዩ ስልቶች የመማር ማስተማሩን ስራ እንዲያስቀጥሉ ማድረግ፣ ይህ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን በየደረጃውና በተዋረድ ክትትል ማድረግ፤
3. ተማሪዎች እጃቸውን አዘውትረውና በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ተቋማት በአስቸኳይ የሳሙና፣ ሳኒታይዘር እና አልኮል አቅርቦቶችን በመግዛት ተደራሽ እንዲያደርጉና እንዲያሰራጩ ማድረግ፤
4. በቤተ መጽሐፍትና በመመገቢያ አዳራሾች መተፋፈግን ለማስቀረት የመቀመጫዎች ጥግግት እንዳይኖር ማድረግና መጨናነቅ እንዳይኖር የአገልግሎት መስጫ ሰዓትን ማራዘም፤
5. ኮንፍረንሶች፣ አውደ ጥናት እና ስብሰባዎች እንዳይኖሩ ማድረግ፣ ቀደም ብለው የታቀዱ ካሉም መሰረዝ፣ ግድ የሚሉ ስብሰባዎች ሲያጋጥሙ ቅርርብና ጥግግት ሳይኖር ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ማካሄድ፤
6. ስለቫይረሱ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ግቢዎች ውስጥ ማዳረስ፤
7. በየተቋማቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚከታተል አንድ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ክትትል ማድረግ፣ የቫይረሱ ምልክት የታየባቸውን ለመጠቆም የሚያስችሉ ስልክ ቁጥሮች በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተዘጋጅተው ጥቆማዎችን የሚቀበሉና ለበላይ አመራሩ ሪፖርት ማድረግ፤
በሁሉም የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት ቀጣይ አቅጣጫ እስከሚሰጥ ድረስ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 7 ያሉትን በየተቋማቱ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም አሳስበዋል።