አቶ ኦርዲን የ12ኛ ክፍል ፈተናን አስመልክቶ ከትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሳካ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ።
በውይይቱ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ጠቁመው ፥ ይህም በተለይ ማጭበርበርንና ስርቆትን ከማስቀረት አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ፥ የክልሉ መንግስትም የሚሰጠው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
መምህራን ወላጆችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ድጋፋቸውን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን ÷ በክልሉ የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ገልጸው በተለይም የፈተና ኩረጃን ከማስቀረትና ተማሪዎችን ከማብቃት አንፃር በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ሀገር አቀፍ የ12ኛ ፈተና እንዲሳካ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሚኒስትሩ በሐረሪ ክልል በነበራቸው ቆይታ በክልሉ ለ2015 የትምህርት ዘመን እየተደረጉ የሚገኙ ዝግጅቶች፣ የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች እየተሰጠ የሚገኘውን የማጠናከሪያ ትምህርት ስራን እንዲሁም የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና የህይወት ፋና ቲቺንግ ሆስፒታልን ተመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!