በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ ከተማ በአንድ መጋዘን ላይ የእሳት አደጋ ተከሰተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ልዩ ቦታው ቤተል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መጋዘን ላይ ድንገተኛ የእሳት አደጋ መከሰቱን የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ የእሳት አደጋው ዛሬ ረፋድ 4፡15 ላይ የፕላስቲክ፣ የዓረቢያን መጅሊስ እና ፍራሽ ማከማቻ መጋዘን ላይ ነው የተከሰተው፡፡
እሳቱን ለመቆጣጠርም የፌዴራል ፖሊስ አድማ ብተና ተሽከርካሪዎች ፣ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እና የአካባቢው ነዋሪዋች ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ጋር ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጋዘኑ ውስጥ የነበሩ ቁሳቁሶች በፍጥነት ተቀጣጣይ መሆናቸው አደጋውን በፍጥነት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው የተናገሩት፡፡
እስካሁን በሁለት ሰራተኞች ላይ በጭስ ከመታፈን ውጭ በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን የገለጹት አቶ ንጋቱ÷የአደጋው መንስኤ እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ