የጠ/ሚ ዐቢይ የአልጄሪያ ጉብኝት ለአገራቱ ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ ነው – የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአልጄሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ ገለጹ።
በአልጄሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአልጀርስ የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም እና ግዙፉን ሳይዳል የመድሃኒት ፋብሪካ የጎበኙ ሲሆን፥ ከአልጀሪያ ፕሬዚዳንት አብዱልመጅድ ታቡኔ ጋርም የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአልጄሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀደም ሲል በአልጄሪያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ለሁለቱ አገራት የትብብር ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የመሪዎቹ ጉብኝት በአገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩንና ውጤታማ ትብብር ስለመኖሩም የሚያረጋግጥ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ሁለቱም አገራት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እልባት እንዲያገኙ በአፍሪካ ህብረት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆኑን ነው የገለጹት።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና አልጄሪያ የኢንዳስትሪ ልማት የተሻለ ዕድገት ለማምጣት ቁልፍ መሆኑን በመገንዘብ እየሰሩበት እንደሆነ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አንድ ሉዓላዊ አገርና ሕዝብ የተፈጥሮ ሀብቱን የማልማት እና የመጠቀም መብት ያለው መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህ መሰረትም የአፍሪካ አገራት መልካም ጉርብትና እንዲኖራቸውና ችግሮቻቸውንም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አልጄሪያ ትደግፋለች ነው ያሉት፡፡