አገልግሎቱ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚለቁ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ ተማሪዎች የስነ ልቦና ጫና እንዲደርስባቸው የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሳሰበ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ÷ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ቅድመ ዝግጅት ስራ ሙሉ በሙሉ በመጠናቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፈተና ዝግጅቱም የተማሪዎችን ልፋት ሊለካ በሚችል ከደህንነት ስጋት ነፃ እንዲሆን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ለፈተና አሰጣጡ ውጤታማነት ከመፈተኛ ቦታ መረጣ ጀምሮ የፈተና ኮዶችን ብዛት ከፍ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በራሳቸው ጥረት ውጤት ለማግኘት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል፡፡
የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ ተማሪዎች የስነ ልቦና ጫና እንዲደርስባቸው የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ዋና ዳይሬክተሩ ያሳሰቡ ሲሆን÷ ለዚህም የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ተማሪዎችና ወላጆችም መረጃዎችን ከተቋሙ እና ከታማኝ የመረጃ ምንጮች ብቻ እንዲከታተሉ መጠየቃቸውን ከትምህር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡