የህዳሴ ግድብ የሲቪል ስራዎች ግንባታ 95 በመቶ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ስራዎች ግንባታ 95 በመቶ መድረሱ የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ሥነ ስርአት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
ታላቁ የኢትዮያጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው ዓመት ለማከናወን ከተያዙ ዐቢይ እቅዶች መካከል በሁለት ተርባይኖች እና ጄኔሬተሮች ኃይል ማመንጨት አንዱ ነው።
አሁን ላይም ይህ ዕቅድ ተሳክቶ በሁለቱም ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት መቻሉን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።
ከለውጡ በኋላ በፕሮጀክቱ ላይ የማስተካካያ እርምጃ ከተወሰደ በሶስት ዓመታት ውስጥ በግድቡ ውስጥ መተከል የነበረባቸው የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ስራዎችን ማጠናቀቅ ተችሏልም ነው ያሉት።
ግድቡን እስከ 141 ሜትር ከፍ በማድረግ ሁለት ሙሌቶችን ማከናወን የተቻለ ሲሆን ሶስተኛው ሙሌት በሂደት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የኤሌክትሮ መካኒካል ፍብረካ እና ተከላ ስራ ወደ 61 በመቶ ከፍ እንዲሁም የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ስራዎችን ወደ 73 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈጻጸም 87 ነጥብ 3 በመቶ ደርሷል ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፥ አጠቃላይ ስራውን በቀጣይ ሁለት አመት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።