የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል በርካታ አውዳሚና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በድብቅ ወደ ሀገሪቱ ያስገባቸውን በርካታ አውዳሚና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በቁጥጥር ስር ካዋላቸው አደገኛና አውዳሚ ፈንጂዎች መካከል፥ በ20 ባለ ሦስት ሊትር የዘይት ጀሪካን ውስጥ የተከማቸ ለፍንዳታ የሚውል ዱቄት እንዲሁም 35 የህንጻዎች፣ የመንገዶችና የታንክ ማውደሚያ ከባድ ፈንጂዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን በሶማሌ ክልል ከባድ ሽብርና በርካታ ፍንዳታዎችን ለማድረስና ከተሞችን ለማፍረስ አቅዶ እንደነበርም የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘከሪያ አብዲ ገልፀዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘከሪያ አብዲ፥ የክልሉ ልዩ ኃይል የህዝብን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅና ለማስከበር ከምን ጊዜውም በላይ በተጠንቀቅ መቆሙንም አስታውቀዋል፡፡
ሰራዊቱ ከአሸባሪው አልሸባብና ከማንኛውም ጸረ ሠላም ኃይሎች ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያከሽፍና የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም ማረጋገጣቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።