Fana: At a Speed of Life!

ከተለያየ አካባቢ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ወገኖች ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር እና የእየሩስ ዓለም ሕጻናትና ማህበረሰብ ከተለያየ አካባቢ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ወገኖች 23 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ለሚገኙ ወገኖች 16 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የማኅበሩ ተወካይ አቶ ማሞ ታደሰ ድጋፉን ለየደብረ ብርሃን ሪጂዮ ፓሊታን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ አስረክበዋል፡፡
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ አቶ ካሳሁን እንደገለጹት በከተማዋ ከ20 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ሰብዓዊ በሆነ ስሜት ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የእየሩስ ዓለም ሕጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሉጌታ ገብሩ እንደገለፁት÷ ድጋፉ ከ8 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ተደራሽ ማድረገሁን ጠቁመው÷ በተለይም በዚህ የክረምት ወቅት ተፈናቃይ ወገኖችን ማሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ በየነ÷ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ችግሩ ሰፊ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በግርማ ነሲቡ እና በዘላለም ገበየሁ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.