በአዲስ አበባ በተለያዩ ስልቶች የተለያየ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲሰ አበባ ፖሊስ ገለጸ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የአዲስ አባበ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት÷ በከተማዋ ዝርፊያ እና ስርቆት ከዕለት ወደ ዕለት ስልቱን እና አካሄዱን እየቀየረ ብዙዎችን መና እያስቀረ ነው ብለዋል።
በቀንም ሆነ በሌሊት ንብረትን ከመውሰድ አልፎ ሕይወትን እስከመንጠቅ የሚደርሰው የዚህ ሕገወጥ ድርጊት ዳርቻ የከተማዋ ነዋሪ ዋነኛ የየዕለት የስጋት ምንጭ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ደይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደተናገሩት፥ የከተማዋ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
በዚህም በመዲናዋ በተለያዩ ስልቶች በዜጎች ላይ የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተከናወነው ሕግ የማስከበር ስራ አዲስ አበባ ከተማን የሽብር ቀጠና ለማድረግ የታሰበውን ሴራ ማክሸፍ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ያስረዱት፡፡
ወንጀለኞች ጥፋት ሲፈጽሙ ከፖሊስ የተሰወረ ቦታን ስለሚመርጡ በፍጥነት መረጃን ማድረስ ከተቻለ ጉዳዩን በቶሎ እልባት መስጠት እንደሚቻልም ኮማንደር ማርቆስ ጠቁመዋል፡፡
በመዲናዋ የሚካሄድ ሌብነትንና መሰል ድርጊቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋለ ፡፡
በሃይማኖት ወንድራድ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!