በጋምቤላ ክልል ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 310 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል 290 ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ሲሆን ከመካከላቸውም ከ70 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሰጠቱ ተገልጿል።
ኮሚሽነር ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት በግብርና፣ በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ነው።
በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ27 ሺህ 850 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ በግብርናው ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ 50 የሚሆኑት ወደ ልማት ስራ መግባታቸውንና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።