በፕሪሚየር ሊጉ ወልቂጤ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፈ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊጉን መምራት የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ወልቂጤ ከተማን ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በሜዳቸው ተሸንፈዋል።
በሌላኛው ጨዋታ በ25 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ሀድያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በዚህም ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የቻለበትን ውጤት በማስመዝገብ ነጥቡን 28 አድርሷል።
በተመሳሳይ ጅማ አባጅፋርን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ 1 ለ 0 በማሸነፍ 5ኛ ደረጃን ማስጠበቅ ችሏል።
በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ሌላኛው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሱዳማ ቡናን ከወላይታ ድቻ አገናኝቷል።
በጨዋታውም ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 5 ለ 3 በማሸነፍ በ27 ነጥብ አራተኛ ደረጃን አስጠብቋል።
በተመሳሳይ በወራጅ ቀጠና ላይ የነበረው ድሬዳዋ በውድድር ዘመኑ ወጥ አቋም ማሳየት ያልቻለውን ሀዋሳ ከተማን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና መውጣት ችሏል።
ድሬደዋ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 3 ለ 1 ያሸነፈ ሲሆን በዚህም በጊዜያዊነት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የሳምንቱ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።