የአፍሪካ ልማት ባንክ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
ባንኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር በሚሠራበት ማዕቀፍ ላይ መወያያታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ÷ በክህሎት ልማት፣ በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ ድጋፍና ተደራሽነት እንዲሁም በመሰል የትብብር መስኮች ላይ የልማት አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል ማረጋገጡንም ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የገለጹት፡፡