Fana: At a Speed of Life!

በ”ቲክቶክ” ከነሐሴው የኬንያ ምርጫ በፊት የጥላቻ መልዕክቶች እየተሰራጩ መሆኑን ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተንቀሳቃሽ ምስል በሚተላለፍበት “ቲክቶክ” ከነሐሴው የኬንያ ምርጫ ቀደም ብሎ የጥላቻ መልዕክቶች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ።

ክብረ-ነክ፣ ግጭት ቀስቃሽ እና የሐሰት ዜናዎች በተንቀሳቃሽ ምስሎች በቲክ ቶክ እየተሰራጩ መሆናቸውን ጥናቱን ያደረገው ሞዚላ ፋውንዴሽን አስታውቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ከምርጫው ጋር የተያያዙ የተንቀሳቃሽ ምስሎችን ይዘት ለይቶ ማገድ አለመቻሉንም የፋውንዴሽኑ ተመራማሪ የሆኑት ኦዳንጋ ማዱንግ ገልጸዋል።

እንደ ተመራማሪው ከ130 በላይ የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በ33 የግለሰብ አካውንቶች እንደተሠራጩና በይዘታቸውም ጥላቻን የሚዘሩ፣ ሤራ የተሞላባቸው፣ አሳሳች ምስሎችን እና ድምፆችን የያዙ እና የተሳሳቱ የፖለቲካ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡

ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ ጥናቱ ይፋ እስከሆነበት ድረስ ከ”ቲክቶክ” እንዳልታገዱና በኬንያውያን ከ4 ሚሊየን ጊዜ በላይ እንደታዩም ነው የተናገሩት።

ባይትዳንስ በተሰኘው ኩባንያ ባለቤትነት ስር የሚተዳደረው “ቲክቶክ” አሁን ላይ በበርካታ ኬንያውያን ዘንድ ተወዳጁ መተግበሪያ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኦዳንጋ ማዱንግ “ቲክቶክ” ሁኔታውን አጢኖ አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ በኬንያ ያለውን በሐሰት መረጃ በቀላሉ ሊበጠበጥ የሚችል የፖለቲካ ምህዳር አዘቅት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ስጋቱን ገልጸዋል፡፡

“ቲክቶክ” በበኩሉ የተሳሳቱ የምርጫ መረጃዎችን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ላይ ማሰራጨት እንደማይፈቅድ ጠቅሶ በቀጣይ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን እየለየ እንደሚያነሳ አስታውቋል፡፡

ስዋህሊን ጨምሮም 30 በሚደርሱ ቋንቋዎች በተለያዩ ቅርፆች የሚተላለፉ መልዕክቶችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንዳሉት የገለጸው “ቲክቶክ” የኩባንያውን ፖሊሲ የሚጻረሩ ተጠቃሚዎቹን እንደሚያግድ ገልጿል፡፡

ያገዳቸው እና ያልተፈቀዱ ተንቀሳቃሽ ምስሎቻቸውን ያነሳባቸው ደንበኞች እንዳሉ ማስታወቁን ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል፡፡

በኬንያ በፈረንጆቹ 2007 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረ ረብሻ 1 ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡና ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ጥናቱ አስታውሷል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.