Fana: At a Speed of Life!

70 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ በዲጅታል መጠቀም እንዲችል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣የካቲት 26፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ ፈረንጆቹ 2025 የተለያዩ አገልግሎቶችን በጂጅታል መጠቀም እንዲችል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ባለፉት 3 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

የጉባኤው ዓላማ በኢትዮጵያ ለዘርፉ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ለንግድ ተቋማትና በቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ግንዛቤ  መፍጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት በቀለ÷ በኢንተርኔት አማካኝነት በኢንቨስትመንት ላይ ሊሰሩ ስለሚችሉ ኢንተርፕራይዝ ሞዴሎች፣ ቴክኖሎጂ እና ድርጅቶች ጠንካራ የኢንተርኔት ሥነ-ምህዳር መሠረት መፍጠር የጉባኤው ተጨማሪ አላማ  ነው ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን ሙሃመድ÷ የዲጅታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረጻ ጀምሮ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ባገናዘበ መልኩ እንዲሰራ እየተደረገ ነው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምን ለማምጣት በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች በቴክኖሎጂ የተመሰረተ የአሰራር ስርዓት ሂደት፣ የውሳኔ አሰጣጥ ፣ የመረጃ ፍሰትና ክምችት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም እስከ 2025 የኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የተለያዩ አገልግሎቶችን በጂጅታል መጠቀም እንዲችል በትኩረት አየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም ይህንን ለማድረግ መንግስት፣ በዘርፉ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የሲቪክ ማህበራት በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ከአለም አቀፍ ኢንተርኔት መር ተቋማት ከፌስቡክ፣ ከሞዚላ እና ሌሎች ድርጅቶች የተወከሉ አካላት እና በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.