Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለአርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዛሬው ዕለት ለአርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን አስረክቧል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አዘጋጅነት “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ርክክብ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች በክልሉ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ውስንነትን ለመቅረፍና የግብርና ሥራን በዘመናዊ መንገድ በመከወን ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛሉ ተብሏል፡፡

በተካሄደው ርክክብ÷ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ አነስተኛ መውቂያ መሳሪያዎች እንዲሁም የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እንደሚገኙበትም ነው የተመላከተው፡፡

በዛሬው ዕለት 136 ትራክተሮች በክልሉ ግብርና ቢሮ በኩል ለስርጭት የቀረቡ ሲሆን÷ ከጥር ወር ጀምሮም 324 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ማስተላለፍ መቻሉ በመርሐ ግብሩ ተገልጿል፡፡

በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ ያለንን የግብርና አቅም ተጠቅመን ምርትን ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል፡፡

ድህነት የሚቀረፈው የአርሶ አደሩን አሠራር መቀየር ስንችል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ይህን ለማሳካትም አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀም ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው÷ እስካሁን በአማራ ክልል ያሉት ትራክተሮችን ከ800 እንደማይበልጡ ጠቁመው÷ በቀጣይ ተጨማሪ ትራክተሮች እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው÷ በግብርናው ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አማራ ክልል ካለው 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር የሚታረስ መሬት ውስጥ 2 ሚሊየን የሚሆነው ለሜካናይዜሽን አመቺ ቢሆንም÷ አሁን ላይ በሜካናይዜሽን የሚለማው ከ280 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥም በርክክብ መርሐ ግብሩ ተገልጿል።

በበርናባስ ተስፋዬ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.