Fana: At a Speed of Life!

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በቅርቡ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እያደረገ የሚገኘው የሰብአዊ እርዳታ የሚመሰገን መሆኑን ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አስታውቀዋል::
 
ምግብና የሰብዓዊ ቁሳቁስ ጭነው የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ሂደት ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
 
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እያደረገች ያለው ጥረት የሚመሰገን መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በሚደረገው ድጋፍ የተሽከርካሪ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዳሬክተሩ፥ ይህንን በማሳካት ረገድ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አስረድተዋል።
 
ሰብዓዊ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ክልሎች በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ሚኒስቴሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አብሮን እንዲሆን እንፈልጋለን ማለታቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
መጪው ጊዜ ክረምት በመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ የተለያዩ ማዳበሪያዎችን ጭነው ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚጓጓዙ ተሸከርካሪዎች መኖራቸውን እንደሚገነዘቡ ገልፀው÷ለሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጉ ተሸከርካሪዎች ስምሪት ላይም ሚኒስቴሩ እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል፡፡
 
ወይዘሮ ዳግማዊት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለሚያደርገው የሰብዓዊ እርዳታ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.