ትዊተር ከ24 ሰአት በኋላ የሚጠፋ የትዊት አይነት አስተዋወቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትዊተር ከ24 ሰዓታት በኋላ የሚጠፋ አዲስ የትዊት አይነት በብራዚል ሙከራ በማድረግ አስተዋውቋል።
አዲሱ የትዊት አይነት ተጠቃሚዎች በስናፕ ቻት እና ፌስ ቡክ ላይ ለ24 ሰአት ከሚያቆዩት የዕለት ውሎ (ስቶሪ) ምስል ወይም መልዕክት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው ተብሏል።
ፍሊትስ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ትዊት ተጠቃሚዎች ማጋራትም ሆነ መውደድ (ላይክ ማድረግ) አይችሉም፤ በተጠቃሚው ግለሰብ ገጽ ላይም አይታዩም ብሏል ኩባንያው።
ከዚያ ይልቅ ከ24 ሰአት በኋላ የጠፋውን መልዕክትም ሆነ ምስል የገጹ ባለቤት ለመገለጫ (ፕሮፋይል ፒክቸር) የተጠቀመውን ምስል በመክፈት ማየት ይቻላልም ነው ያለው።
አዲሱ ሙከራ ሰዎች ድንገተኛና ትዊት ለማድረግ ያልፈለጓቸውን ሀሳቦች እንዲጋሩ ሊረዳቸው ይችላልም ብሏል።
ትዊተር ላለፉት በርካታ ወራት ተገልጋዮቹን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮችን እየተገበረ ቢሆንም የኩባንያው እድገት ከተወዳዳሪዎቹ አንጻር ወደ ኋላ የቀረና ፈጠራ የጎደለው እንደሆነ ይነገራል።
ምንጭ፦ ሬውተርስ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision