የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ለጊዜው ያዘገየውን ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት ድጋፍ አስመልክቶ ሊወያይ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ለጊዜው ያዘገየውን ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ በቀጣይ ወር ሊመክርበት ቀጠሮ መያዙን የኅብረቱ የሰብዓዊ መብት ተወካይ ኢሞን ግሊሞር ተናገሩ።
የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብት ኢሞን ግሊሞር በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመመልከት በኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸውም ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶችን እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
ጉብኝታቸውም በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከእነዚህ አካላት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ተወካዩ የጠቆሙት።
በዚህም በተለይም ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የተደረሰው የተኩስ መቆም ውሳኔ ኅብረቱ በአዎንታ እንደሚቀበለው ገልጸው ፥ ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው ፥ የሰብዓዊ ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ከዚህም አንጻር የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው ፥ ለዚህም ሙሉ ፍቃደኛ ነው ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት ድገፍ ገንዘብ ጨምሮ ለጊዜው ማዘግየቱን ገልጸው ፥ ጉዳዩ እየተጤነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤትም ለጊዜው ያዘገየውን ለኢትዮጵያ የሚያቀርበውን የልማት የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ በቀጣይ ወር ሊመክርበት ቀጠሮ መያዙንም ነው የገለጹት።
ምክር ቤቱ እርሳቸው የሚያቀርቡት ሪፖርት ተመርኩዞም በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አጠቃላይ ግምግማ በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ኢሞን ግሊሞር በመግለጫቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት፣ በአገራዊ ምክክርና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን እንደሚመለከት ጠቁመዋል።
መንግሥት በየትኛውም አካባቢዎች የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ አጥፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ ፍትህ ለማስፈን የሚደረገውን ጥረትም ምክር ቤቱ በውይይቱ ይመለከተዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው አገራዊ ምክክርም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደው የሠላም ሂደት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።
በቀጣይ ዓመት በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ኅብረት በሰብዓዊ መብትና በማኅበራዊ መብት ዙሪያ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ስብሰባ እንደሚካሄድ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።