በበጋ መስኖ በሁለት ዙር 600 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ተሸፍኗል – የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጋ መስኖ በሁለት ዙር 600 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ከፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው መሬት እስከ 24 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
ሰፋ ያሉ የማምረቻ ማሳዎችን ይዘው የተለያዩ ሰብሎችን የሚያመርቱ የግል ባለሀብቶችን በመደገፍ እና በማሰማራት የምርት አቅርቦቱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
የበጋ መስኖን በመጠቀም ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት÷ የምርት አቅርቦቱን በማስፋት የኑሮ ውድነቱን ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከወኑ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በሚመረተው ስንዴም ሆነ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያን በማረጋጋት በኩል የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በገበያ ላይ የሚታዩ ሰው ሰራሽ እጥረቶችን መፍታት መቻል እና የግብይት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አሁን እየተሰራ ያለው የስንዴ ልማትን በቀጣይ አመት በማጠናከር እስከ 1 ሚሊየን ሄክታር በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከውጭ የሚገባን ስንዴ ሙሉ በሙሉ የማስቅረት እቅድን ለማሳካት ይሰራል ብለዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን