በቤንች ሸኮ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ በሰጡት መግለጫ÷ በክልሉ በሶስት ዞኖች የወባ ስርጭት ቢኖርም በቤንች ሸኮ ዞን ያለው ስርጭት በፍጥነት እየጨመረና ወደ ወረርሽኝነት እየተጠጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ መስጠት ባለሙያ አቶ እሸቱ ወልደሚካኤል በበኩላቸው÷ “በዞኑ ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ምርመራ በወባ የመያዝ ምጣኔ 49 በመቶ ደርሷል” ብለዋል፡፡
የወባ ስርጭቱ በተለይ በሚዛን አማንና በጉራፈርዳ ወረዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ በሚዛን አማን ከተማ በወባ የመያዝ ምጣኔው 64 በመቶ ሲሆን በጉራፈርዳ ወረዳ ደግሞ 69 በመቶ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዞኑ ከጥር 2014 ጀምሮ በተደረገ ምርመራ 15 ሺህ 378 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው የተመላከተ ሲሆን÷ በሽታው ከተገኘባቸው መካከል 3 ሺህ 180 ከጉራፈርዳ እና 1 ሺህ 898 የሚሆኑት ደግሞ በሚዛን አማን ከተማ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘውን የወባ በሽታ ለመቀነስ በመከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
በተስፋዬ ምሬሳ