የህንድ ተቋማት አገራቸው ያካበተችውን የዳያስፖራ ተሳትፎ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ ለረጅም ጊዜ ያካበተችውን የዳያስፖራ ተሳትፎ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማጋራትና በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የህንድ ተቋማት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የልምድ ልውውጥ ለማከናወን ህንድ ተገኝቷል፡፡
አገልግሎቱ ከጂ አይ ዜድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የዳያስፖራውን ተሳትፎ ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ በመላክ፣ በኢንቨስትመንት፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳደግ በሚቻልባቸዉ ሁኔታዎች ላይ የህንድን ተሞክሮ ለመቅሰም በአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ የተመራ የልዑካን ቡድን ለአምስት ቀናት ጉብኝት አድርጓል።
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው በህንድ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ በውጭ የሚኖሩ የህንድ ዜጎች ጉዳዮች ተቀዳሚ ፀሀፊ ማኒካ ጄይንን እና በንግድ ዲፓርትመንት የአፍሪካ አህጉር የውጭ ንግድ ዘርፍ የጋራ ፀሃፊ ሽሪካር ሬዲ ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂዎች፣ የመንግስት አስተዳደር አካሄዶች፣ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት እና የንግድ ማበረታቻዎች፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዳያስፖራ ማፒንግ ስራ፣ የዳያስፖራ መረጃ እና የመንግስት መረጃ አያያዝ ስርዓቶች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም የልኡካን ቡድኑ ከህንድ ሪዘርቭ ባንክ የስራ ኃላፊዎች ጋር በዳያስፖራ የገንዘብ ልውውጥ አስተዳደር ዘዴዎች ላይ የተወያየ ሲሆን÷ ከሀሪና ግዛት የውጭ ትብብር መምሪያ አስተባባሪነትም ከህንድ ዳያስፖራ ባለሃብቶች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል።
ህንድ ባለፉት 20 ዓመታት ያካበተችውንና አሁን የደረሰችበትን የዳያስፖራ ተሳትፎ ተሞክሮ በመጠቀም ኢትዮጵያ ዳያስፖራዋን በኢንቨስትመንት ፣ በንግድ፣ በሬሚታንስ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ይበልጥ ለማሳተፍ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍና አብሮ ለመስራት ተቋማቱ ዝግጁ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!