ጉዳት የደረሰባቸው የህክምና ተቋማትን እስራኤል ከሚገኙ የህክምና ተቋማት ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን አሰራር ለመዘርጋት መታሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከእስራኤል ከመጡ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡
ልዑካን ቡድኑ የእስራኤል ፓርላማ አባላትና በሀገሪቱ ባሉ እውቅ ሆስፒታሎች የሚሰሩ የህክምና ባለሞያዎችና ሃላፊዎች ናቸው፡፡
በህክምና ዘርፉ ኢትዮጵያን ለማገዝ ዓላማ አድርገው የመጡት ልዑካኑ፥ በጦርነቱ የተጎዱ የህክምና መስጫ ተቋማትን፣ የተቋማቱን አገልግሎት አሰጣጥና የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎብኝተዋል፡፡
ከጉብኝታቸውም በርካታ የስብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች መኖራቸውን ተገንዝበናል ብለዋል ልኡካን ቡድኑ አባላት፡፡
በመሆኑም በተለይ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመደገፍ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው የህክምና ተቋማትም እስራኤል ከሚገኙ የህክምና ተቋማት ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን አሰራር ለመዘርጋት ታስቧልም ብለዋል::
ልዑካን ቡድኑ ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሆኑ ቤተ እስራኤልያዊያን በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በማንኛውም ሁኔታ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዲማ ነገዎ ፥ ሀገራቱ የረዥም ጊዜ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው በማንሳት ኢትዮጵያን ለማገዝ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
እስራኤል በርካታ ልምድ ባካበተችባቸው በሌሎች የግብርናና የትምህርት ዘርፎችም ኢትዮጵያን እንዲያግዙ የጠየቁ ሲሆን ፥ በኢንቨስትመንቱም የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ፀጋ ተጠቅመው እንዲሳተፉ ጋብዘዋል፡፡
ሌሎች የፓርላማ አባላትም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጋር የተከሰተ ድርቅ መኖሩን አንስተው ፥ እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ልዑካን ቡድኑም ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኃላ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘርፎች ለማገዝ ፍቃደኛ መሆናቸውን አንስተው ፥ በነበራቸው ቆይታም እጅግ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በምሽቱ መርሃግብርም ከጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘቢብ ተክላይ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!