ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በምግብ ዋስትና ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከሩስያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በምግብ ዋስትና ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተፈጥሮ ጋዝ ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ በእርሻ ምርታማነት ላይ ዓይነተኛ ድርሻ ባላቸው በአፈር ማዳበሪዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መናር ማስከተሉን ነው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ የገለጹት።
ዋና ዋናዎቹ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ማለትም የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የዓለም ንግድ ድርጅት÷ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመሻገር እንዲያስችል ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በምግብ ዋስትና ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
ተቋማቱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም በችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ድሃ አገሮች በምግብ አቅርቦት፣ በገንዘብ ድጋፍ፣ የግብርና ምርትን በመጨመር እና በመሳሰሉት መንገዶች የፋይናንስ ፍላጎታቸውን ለመሸፈን በተቀናጀ መልኩ በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት።
የሩስያ- ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱን ከያዘው ዓለማቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ እና ከአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ ኢኮኖሚውን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል ይላሉ የገንዘብ ተቋማቱ፡፡
የኢኮኖሚ ቀውሱ አብዛኛውን የምግብ ፍጆታቸውን ከውጭ ለሚያስገቡ ድሃ ሀገራት የከፋ መሆኑን የጠቀሱት ተቋማቱ፥ ሆኖም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራትም ቢሆኑ ከችግሩ ተጋላጭነት አልዳኑም ነው ያሉት፡፡
የናይትሮጂን ማዳበሪያ ዋነኛ ግብአት የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ምክንያት በዓለማቀፍ ደረጃ የማዳበሪያ ዋጋ መናሩንም ተቋማቱ ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ተቋማቱ ያላቸውን የእውቀት እና የገንዘብ አቅም በመጠቀም ተጋላጭ ሀገራትን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል ሲል አናዶሉ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!