ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን – በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 4 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ በዛሬው ዕለት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጎብኝተዋል፡፡
አምባሳደር ያፕራክ አልፕ በጉብኝታቸው የፋና የቴሌቪዥን፣ የኤፍ ኤም 98 ነጥብ 1 ስርጭት ማዕከል እና ሌሎች የመገናኛ አማራጮችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ለአምባሳደሯ ባደረጉት ገለጻ፥ ፋና በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወቅታዊ እና ተዓማኒ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ቀዳሚ ሚዲያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተቋሙ አዝናኝ እና አስተማሪ የሆኑ ፕሮግራሞችን በሁሉም የመገናኛ አማራጮች ለአድማጭ ተመልካቾች ከማድረሱም ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ነው ያስረዱት።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአገራችንን መልካም ገፅታ ለውጪው አለም ሊያስረዱ ከሚችሉ የሚዲያ ስራዎች ባሻገር በሚዲያው ዘርፍ ጥልቅና ሰፊ ልምድ ካላቸዉ አገራት ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ልምዶችን ይቀምራል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የአምባሳደሯ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን መጎብኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ከማጠናከር በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና አስፈጻሚ አቶ አቤል አዳሙ በበኩላቸው፥ ፋና በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ እና በዲጅታል ሚዲያ አማራጮች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ተዓማኒ፣ ሚዛናዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝቡ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቱርክ በሚዲያው ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያላቸው ሚዲያዎች ያሉባት አገር መሆኗን አንስተው፥ ፋና ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ያፕራክ አልፕ በበኩላቸው፥ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተለያዩ ቋንቋዎችን እና የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም ለማህበረሰቡ ተዓማኒ፣ ሚዛናዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማሰራጨት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡
ፋና በገነባው የሚዲያ ስርጭት ማዕከል የጥራት እና የቴክኖሎጂ ደረጃ እንደተደነቁ በመግለፅ፥ በይዘት ዝግጅትም እያከናወነ ያለውን መልካም ስራዎች እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ቱርክ እና ኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደሯ፥ በቀጣይ ሁለቱን አገራት በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ ለማስተሳሰር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ኤምባሲው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡