Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል – ዶ/ር ቴድሮስ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ እና ዓለም አቀፍ ስጋት ሊሆን የሚችልበት አቅም ላይ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለፁ።

የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አስተያየት የተሰማው በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ባለፉት ሁለት ቀናት ከቻይና በበለጠ በሌሎች ሀገራት አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውም ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ከቻይና ውጭ ኢራን እና ጣሊያን የቫይረሱ መገኛ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ቫይረሱም ከእነዚህ ሃገራት ወደ ሌሎች ሀገራት በሚያቀኑ ሰዎች አማካኝነት እየተሰራጨ ነው ተብሏል።

ዶክተር ቴድሮስ በሰጡት አስተያየት በቀሪው ዓለም እየታየው ያለው ነገር አሁን ላይ ትልቅ ትኩረት የምንሰጠው ነው ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የዓለም መንግስታት ቫይረሱን ለመቆጣጠር በፍጥነት እና በጥንካሬ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ወቅቱ የፍርሃት ሳይሆን ቫይረሱን የመቆጣጠር እና የሰዎችን ህይወት የምናተርፍበት ጊዜ ነውም ብለዋል ዶክተር ቴድሮስ በንግግራቸው።

ከቻይናዋ ውሃን ከተማ የተነሳው የኮሮና ቫይረስ አሁን ላይ የስርጭት አድማሱን እያሰፋና የሃገራት ትልቁ ስጋት እየሆነ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.