Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ ክትባት ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 3፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ ክትባት ሊሰጥ መኾኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

ለዘመቻው ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና እና ወላጆች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት አማካሪ ባለሙያ ሙሉጌታ አድማሱ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ ከጎረቤት ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልልም ምዕራብ ጎጃምና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን  ባለፈው ዓመት ተጠርጣሪዎች መገኘታቸውን ጠቅሰው፥ በክልሉ 12 ዞኖች ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት በዘመቻ መስጠት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የመጀመሪያው ዙር ክትባት በደሴ ከተማ አሥተዳደር፣ በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለመሰጠቱ በሁለተኛው ዙርም እንደማይሰጥ ነው ባለሙያው የገለፁት፡፡

በመኾኑም ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕጻናት መደበኛ ክትባት ቢከተቡም እንኳ በዘመቻ የሚሰጠውን ክትባት ማስከተብ እንደሚገባ አቶ ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡

አሁን ላይም የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት የተሳተፉበት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.