ማዕቀብ ችግር ያጋጠማቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን የሚጎዳ ነው-ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ማዕቀብ የሰብዓዊ ቀውስን ያባብሳል፤ ችግር ያጋጠማቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ይጎዳል ሲል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ተናገረ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን በአዎንታ እንደሚመለከተው ተቋሙ ገልጿል።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑክ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፋቲማ ሳቶር ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ተቋሙ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ከተከሰተ ጀምሮ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በችግር ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን የህክምና፣ የምግብና የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡ መንግሥት ያደረገውን ግጭት የማቆም ውሳኔ ተቋሙ በአዎንታ እንደሚመለከተው ገልጸው፥ ይህም የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ ይረዳል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ ማስቀል ኮሚቴ ባለፉት ሁለት ወራት 40 የሕክምና ድጋፍ የያዙ በረራዎች ወደ ትግራይ ክልል ማድረጉንም ገልጸዋል።
ተቋሙ በሶማሌ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ለሚገኙ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከብቶች የክትባትና የመኖ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን ድጋፉን ለማቀላጠፍ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተቋሙ በችግር ላይ ለወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች የህክምና ቁሳቁስ፣ የምግብና የውሃ መሳቢያ መሳሪያዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ይህንንም የድጋፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውንም አዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!