በድሬዳዋ ከአንዲት ታዳጊ ሕፃን አምስት ኪሎ የሚመዝን ዕጢ ወጣ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ደደር ወረዳ ሐቀባስ ቀበሌ ነዋሪ ከሆነች የ10 ዓመት ታዳጊ ሕፃን አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕጢ በቀዶ ጥገና ወጣ፡፡
ከአንድ ወር በፊት ሆዷ አካባቢ እያደገ የሚሄድ እብጠት አጋጥሟት የነበረችው ታዳጊ እንደ እኩዮቿ ተራሩጣ መጫወትና መንቀሳቀስ ባለመቻሏ አልጋ ላይ አውሏት እንደነበር ቤተሰቦቿ ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በድሬዳዋ አርት ጀኔራል ሆስፒታል ለአንድ ሰዓት በፈጀ የቀዶ ጥገና እጢውን ያወጡት ረዳት ፕሮፌሰር ታምር ንጉሴ እጢው አንጀቷ አካባቢ የበቀለ መሆኑን ገልጸው ወደ ሕክምና በምትመጣበት ወቅትም የደም ማነስ እንደነበራት አስታውቀዋል፡፡
እጢው ለተጨማሪ ምርመራ ናሙናው መላኩንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እጢው በቀዶ ጥገና በተወገደበት ወቅት በውስጡ ከነበረው ፈሳሽ ጋር 5 ኪሎ ግራም ይመዝን የነበረ ሲሆን ፈሳሹ ከተወገደ በኋላ እጢው ብቻውን ወደ ሦስት ኪሎ ግራም መመዘኑን አስታውቀዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ